Thursday, May 1, 2014

ተጨማሪ መረጃዎች በህገ ወጡ መጅሊስ መፈንቅለ ስልጣን ዙሪያ!


ድምፃችን ይሰማ 


ሐሙስ ሚያዝያ 23/2006

በትናንቱ ሰበር ዜና በህገ ወጡ የፌደራል መጅሊስ ውስጥ የተደረገው መፈንቅለ ስልጣን ፕሬዝዳንቱን እስከማባረር መድረሱን ለማየት ተሞክሯል፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችን እነሆ!

የውዝግቡ ምንጭ በየካቲት አጋማሽ በድሬዳዋ ከተማ ላይ በተደረገው 11ኛው የመጅሊስ ጠቅላይ ጉባዔ ላይ የተሰጠው የአቋም መግለጫ ሲሆን በአቋም መግለጫው ላይ የተካተቱት አንዳንድ ነጥቦች መጅሊሱ ውስጥ ‹‹ለዘብተኛ›› አቋም የያዘውን ቡድን ለማግለልና ለማባረር ያቀዱ መሆናቸውም ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

የአቋም መግለጫው መንስኤ መንግስት ከህዝበ ሙስሊሙ ፍላጎት ውጭ በመስከረም 27/2005 በቀበሌዎች ባካሄደው ህገ ወጥ የመጅሊስ ምርጫ ወደስልጣን ያመጣቸው አካላት ሁሉም በእኩል ደረጃ ጸረ-ሙስሊም አጀንዳውን ሊያስፈጽሙለት ባለመቻላቸው አካሄዱን እየተቃወሙት ያሉትን የአመራር አባላት ለማስወገድ ያለው ፍላጎት ነው፡፡ በአቋም መግለጫው ላይ በተካተቱት ነጥቦች መሰረት በተለይ መጅሊሱ በክልል ደረጃ ባለው ስልጣን የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ውክልና ማንሳት እንዲችል መደረጉ (ነጥብ 4) ከመተዳደሪያ ደንቡ ጋር በግልጽ የሚጋጭ ሲሆን ይህም ‹‹እንዲወገዱ የፈለጋቸውን ሰዎች ያለ ህጋዊ ሂደት ማባረር እንዲችል መንገድ ይከፍታል›› የሚል ተቃውሞ እንዲነሳበት አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በአቋም መግለጫው 1፣ 3፣ 4፣ 5 እና 10ኛ ተራ ቁጥሮች ላይ የተንጸባረቁት ሌሎች ነጥቦች፣ ማለትም አመራሩ ራሱን ከ‹‹አክራሪ››፣ ‹‹ወሐቢያ››፣ ‹‹ኢኽዋን›› እና ‹‹ተክፊር›› ማጥራትና ‹‹ጽንፈኞችን›› ማባረር እንዳለበት ከተቀመጠው ነጥብ ጋር ተዳምሮ መንግጅሊሱ ለሚያስፈጽመው የመንግስት እኩይ አጀንዳ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን የማስወገድ መብት ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ‹‹መጅሊሱ ሁሉንም አስተሳሰቦች አቻችሎ ቢሄድ ነው የሚሻለው›› የሚል አቋም ያራመዱትንና በትናንትናው እለት መፈንቅለ ስልጣን የተደረገባቸውን አባላት ከአክራሪው መፍቅሬ-አህባሽ ቡድን ጋር ካወዛገቡት ነጥቦች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ሌላው በአቋም መግለጫው ላይ መካተቱ የውዝግብ ምንጭ ያደረገው ነጥብ ደግሞ ከመንግጅሊሱ ቀጣይ እንቅስቃሴና አህባሽን አስገድዶ የመጫን ሂደት ጋር ተያይዞ የተያዘው አቋም ሲሆን ለዘብተኛው የአመራር ቡድን ‹‹መጅሊሱ ዳግም የህዝበ ሙስሊሙን ተቃውሞ ሊያገረሹ ከሚችሉ አካሄዶች መቆጠብ አለበት›› የሚል አቋም በመጅሊሱ ውስጥ ማራመዱ ጥርስ አስነክሶበታል፡፡ ይህ ቁጥብነት ከፌደራል ጉዳዮች ቀጥተኛ ትእዛዝ ብቻ በመቀበል እየተንቀሳቀሱ ላሉት መፍቅሬ-አህባሽ ቡድኖችም ራስ ምታት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም በተቋሙ ስም መንግስት ያሻውን እንዳይፈጽም እንቅፋት የሆኑበትን አካላት ሁሉ ካሁን ቀደም ለረጅም ጊዜ በመጅሊሱ ውስጥ ሲያደርገው እንደቆየው ‹‹ውክልና ማንሳት›› የምትባለውን ዘዴ በመጠቀም ‹‹ለዘብተኞቹን›› ከጨዋታ ውጭ አድርጓቸዋል፡፡ በመጅሊሱ ታሪክ በአጋጣሚም ሆነ ባለማወቅ ከመንግስት ቁጥጥር ወይም ፍላጎት ውጭ በመጅሊሱ መዋቅር ውስጥ የገቡ አካላት፣ አልያም በመንግስት ፍላጎት ገብተው ኋላ ላይ ከመንግስት የተለየ አቋም ሲያራምዱ የተገኙ አመራር አባላት ሲወገዱ የነበረው በዚሁ ዘዴ ነበር፡፡ ዛሬም ያንኑ ያረጀ ስልት ራሳቸው በቀበሌ የ‹‹ቅርጫ›› ሂደት መርጠው ባቋቋሙት ህገ ወጥ ካቢኔ ላይ ደግመውታል - ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ!

በጉዳዩ ላይ የህዝበ ሙስሊሙ አቋም ግልጽ ነው፤ ህዝበ ሙስሊሙ መሪዎቹን ራሱ መምረጥ ይፈልጋል! በመጅሊሱ ውስጥ ከህዝብ እውቅናና ፍላጎት ውጭ ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ ለዘብተኛም ሆነ ጽንፈኛ መሪዎች መምጣታቸውን ያወግዛል! መረዎቹን መምረጥ ያበት ህዝበ ሙስሊሙ ራሱ ብቻ ነውና!

(ከታች በመፈንቅለ ስልጣኑ የተባረሩት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ሸኽ ሙሀመድ አማን በድሬዳዋው ጉባዔ የጸደቀውን የአቋም መግለጫ ተቃውመው ለተለያዩ የመንግስት አካላት በመጋቢት 26 እና 29/2006 የጻፏቸው ሁለት ደብዳቤዎች እና በድሬዳዋው ጉባዔ የተላለፈውን የአቋም መግለጫ የሰፈረበት የፎቶ አልበም ተያይዟል)

https://www.facebook.com/media/set/?set=a.747502598634432.1073741858.324725940912102&type=3&uploaded=9

ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ህገ ወጥ መጅሊሱ የሚገኝበትን ሁኔታ አስመልክቶ ፕሬዝዳንቱ ሸኽ ኪያር የጻፉት ደብዳቤ Page 1 of 3

No comments:

Post a Comment