የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል መሪ የሆነው ''ድምፃችን ይሰማ'' የፌስቡክ ፔጅ
ለአዲሱ የትግል ምዕራፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴውን ጀመረ!!!
''ድምፃችን ይሰማ'' አዲሱን የትግል ምዕራፍ አስመልክቶ ህዝበ ሙስሊሙ የጋራ
ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል::
መልዕክት ቁጥር 1 እነሆ!
አዲሱን የትግል ምእራፍ አስመልክቶ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን የተላለፈ መልዕክት - ቁጥር 1ለውጥ፤ ተፈጥሯዊ ሂደት!
ቅዳሜ ሚያዝያ 18 /2006
ምድር ህላዌዋ ከተቦካበት ቅፅበት አንስቶ በለውጥ ምህዋር ላይ እየተሸከረከረች ትገኛለች፡፡ ቀኑ ሰዐቱን ጠብቆ ሲመሽ ብርሀን በጨለማ ይለዋጣል፡፡ ምሽቱ ተራውን ለቀን ሲያስረክብ ደግሞ ጨለማው በብርሃን ይለወጣል፡፡ ምድር ሁሌም በለውጥ ሀዲድ ላይ ትከንፋለች፡፡ ዛሬ ከትላንት፣ ነገም ከዛሬ ለውጥን ይቀባበላሉ፡፡ የሰው ልጅ የህይወት ዑደት ስለ ለውጥ ተፈጥሮዊነት አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ከአንቀልባ እስከ ከፈን በሚዘረጋው የህይወት ጅረት የሰው ልጅ ሲፈስ በበርካታ የለውጥ ድልድዮች ስር ያልፋል፡፡
የታሪክ መዘውርን ስንቃኝም ይህንኑ አውነታ ነው የምናገኘው፡፡ ለዚያም ነው ነብያት ይዘወት የሚመጡት አስተምህሮ ይዘት ወጥ ቢሆንም አፈፃፀሙና ቅርፁ ግን የለውጥን ተፈጥሯዊነት ባገናዘበ መልኩ የተቃኘና ከየወቅታዊው ተጨባጭ ጋር እንዲገጥም የተለያየ የሆነው፡፡
የሰውን ልጅ የታሪክ ምዕራፍ ሰፊውን ቦታ የሚሸፍነው ትግል ነው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የሰው ልጆች በግልም ይሁን በህብረት ለተለያየ አላማና ግብ ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ትግሎች ጭቆናን ለማሰወገድ የተደረጉ ሲሆኑ መነሻና መድረሻቸው የተራራቀ ቢሆንም ሁሉም ለውጥ በተባለ ተፈጥሯዊ ምህዋር ላይ ግን አልፈዋል፡፡ የትግሎች መወለድ፣ የአድማሳቸው መስፋት፣ መጎልበት፣ ብሎም ወደ ስኬት መዳረሻ የሆኑ ጎዳናዎችን እንደተጨባጩ መቀያየር የተፈጥሯዊው ለውጥ አንድ አካል ነው፡፡ ያለ ለውጥ ውጥናቸውን ያሳኩ ትግሎች፣ የድል ደጃፍ የደረሱ እንቅስቃሴዎች በታሪክ ማህደራት ውስጥ አይገኙም፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላለፉት ሁለት አመታት በእምነታችን ላይ የተቃጣውን ዕኩይ ተልዕኮ ለመመከት በትዕግስት፣ በፅናትና በቁርጠኝነት እየታገልን እንገኛለን፡፡ በዚህ የትግል ሂደት ከመባቻው ጀምሮ ነባራዊ ሁኔታውን ባማከለ መልኩ በተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ አልፈናል፡፡ የመጀመሪያው የትግል ሂደት ውስንና ተጨባጩ በፈቀደው መልኩ በአንድ ቦታ በመሰባሰብና በመወያየት ጭምር የነበረ ሲሆን እርከኑን ጠብቆ በማደግ በአንድ ቅጥር ግቢ ከመወሰን ዘልሎ ሁሉንም ማዳረስ የቻለውም ተፈጥሯዊውን የለውጥ ዱካ ተከትሎ ነው፡፡ የመንግስትን መዋቅር ተከትሎ አቤቱታዎችን ከማስገባት ሂደቱ ጎን ለጎን ብቅ ያለው የመስጂድ ተቃውሞም የዚሁ የለውጥ ፍሬ ነው፡፡ ቅርፃቸው የተለያዩት የተቃውሞ ሂደቶችና መርሀ-ግብሮች ተለዋዋጩ ነባራዊ ሁኔታ የወለዳቸው ናቸው፡፡ ከኮሚቴዎቻችን በግፍ መታሰር ማግስትም ትግላችን የይዘት ሳይሆን የቅርፅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ የትግሉ ባለቤት የሆነው ህዝበ ሙስሊሙ ንቃትና ብሰለት ከዕለት ወደ ዕለት ዕድገትና ለውጥ ማሳየት፣ ብሎም የሀገሪቱ እና አለም አቀፍ ተጨባጭ መቀያየር በተለያዩ ጊዜያት ትግሉ ለውጥ እንዲያመጣ የበኩላቸውን ተፅዕኖ አሳርፈዋል፡፡
ዛሬ ላይም ያነሳናቸውን ጥያቄዎች መንግስት ለመመለስ ፍቃደኛ አለመሆኑን መሰረት አድርጎ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እየከፈለ ላለው መስዕዋትነት የሚመጥን ተገቢ የሆነ ሰፊ አጀንዳ ማስቀመጥ ተፈጥሯዊው የለውጥ ምህዋር የሚወልደው ተሀድሶ በመሆኑ በዚያው መስመር በአላህ ፈቃድ መፍሰሳችንን እንቀጥላለን!
የትግል አቅጣጫ ማስገንዘቢያ መልእክቱን የድምጽ ትረካ ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡-
http://goo.gl/PtMfJt
ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment