Tuesday, April 29, 2014

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል መሪ የሆነው ''ድምፃችን ይሰማ'' የፌስቡክ ፔጅ

 ለአዲሱ የትግል ምዕራፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ ጀመረ!!!

''ድምፃችን ይሰማ'' አዲሱን የትግል ምዕራፍ አስመልክቶ ህዝበ ሙስሊሙ  የጋራ

 ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል::

መልዕክት ቁጥር 4 እነሆ! 

#EthioMuslimStruggle 
አዲሱን የትግል ምእራፍ አስመልክቶ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን የተላለፈ መልእክት - ቁጥር 4

የቀጣዩ የትግል እርከን መነሾዎች!
ማክሰኞ ሚያዝያ 21/2006

በሃምሌ 2003 የአህባሽ ጠመቃ ዋነኛ መንስኤነት የተጀመረው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን የመብት ማስከበር ትግል ትላልቅ እርከኖችን አልፎ መጥቷል፡፡ አሁን ወደ ቀጣዩ እርከን የሚሸጋገርበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን በነበረው ሂደት ትግሉ ይዞት ከተነሳቸው ሶስት ጥያቄዎች አለመመለስ ውጭ እጅግ ውጤታማ ሂደት ነበር፡፡ ምናልባት ጥያቄዎቹ ቢመለሱ ሊሰጡት ከሚችሉት ጥቅም በላይ ሌሎች ትልልቅ ፋይዳዎችን ለኡማው አበርክቷል፡፡ ከውጤቶቹ አንዱ ደግሞ ህዝባችን መብታችንን ማስከበር እና ከውስጥ ጉዳያችን የመንግስትን ጣልቃ-ገብ እጆች ማስወጣት ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ በይፋ መናገር የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ነው፡፡

መንግስት ጥያቄዎቹን ላለመመለስ እየተከተለው ያለው አካሄድ ሙስሊሙ እንደዜጋ ከሚጋፈጣቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተጨማሪ እምነቱን ብቻ መሰረት ያደረገ ነጥሎ የማጥቃት ዘመቻውን በዕቅድ ይዞ እንደሚሰራው መላው ህዝብ በማያሻማ ሁኔታ መረዳቱ ለዚህ ደረጃ መደረስ ዋና ምክንያት ነው፡፡ የጥያቄዎቻችን ቀላል ይዘት፣ ያቀረባቸው መላው ሙስሊም ከመሆኑ እና ከሁለት አመታት በላይ በፅናት ከመዝለቁ ጋር ተዳምሮ መልስ ሊነፈግ የቻለው በአንድ እና አንድ ምክንያት ነው፡- ይኸውም ሃምሌ 2003 ይፋ የሆነው የመንግስት ዕቅድ የአጠቃላይ ዘመቻው አንዲት ማሳያ ብቻ በመሆኑ! ይህ ማሳያ ፊት ለፊት የሚታገል ህዝብ ባያጋጥመው የት ድረስ እንደሚጓዝ መገመት አይከብድም፡፡ በትግል ውስጥ ላለ አንድ ማህበረሰብ ደግሞ ይህንን መረዳት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ሰላማዊ የመብት ትግላችን ሶስት ውስን ጥያቄዎችን አስቀድሞ ሲመርጥ ጥያቄዎቹ የሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ብቸኛ ሃገራዊ አጀንዳዎች ስለሆኑ አልነበረም፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የመታገል አቅም እና አካሄድ ‹‹አምባገነኖችን ተክቼ ፍትህን በየደረጃው ለማስፈን ቆሜያለሁ›› የሚልን መንግስት ሶስት ጥያቄዎችን እንዲመልስ ለማድረግ እንደማያንስ አስቀድሞም ይታወቅ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹን ውስን ማድረግ ግድ የሆነው መንግስት ሃገር ለማስተዳደር፣ ህዝብ ደግሞ ሙሉ ዜግነት እንዲሰማው መሟላት ያለባቸው መሰረታዊ መብቶች ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ማህበረ-ፖለቲካ ጉዞ ጋር እንደሚፈቱ በማመን ነበር፡፡ እነዚህ መሰረታዊ መብቶች አሁንም ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ሂደት ጋር ተዳምረው የሚታዩ ቢሆንም ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ መብቶቹን ከሌላ አካል እንደሚበረከቱለት ገፀ በረከቶች አድርጎ የሚጠብቅበት እድልም ተስፋም አግባብም እንደሌለ የሁለት አመት ሰላማዊ ትግላችን ጥርት ባለ መልኩ አሳይቶናል፡፡

ዛሬ ላይ ባነሳቸው ውስን ጥያቄዎች ሽፋን እየተገፈፉ የመጡት ሌሎች መሰረታዊ መብቶች አካሄዳቸውን ለመቀልበስ የማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ህዝበ ሙስሊሙ እውነታውን ሊረዳ፣ ተረድቶም ተግባራዊ እርምጃ ሊወስድ ግድ ይለዋል፡፡ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄም ነው፡፡ ከሁለት አመታት በፊት ከህዝብ ከተሰበሰቡት በርካታ ጥያቄዎች ሶስት ሲመረጡ በወቅታዊነታቸው፣ በአንገብጋቢነታቸው መሆን ያለባቸው እና መሆን የሚችሉ እንደሆኑ በመታመኑ ነው፡፡ እነዚያ ጥያቄዎቻችን ዛሬም አንገብጋቢ እና መሆን ያለባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን እነሱ እውን እንዲሆኑ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ማድረግ የወቅታችን ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ግድ ነው፡፡

ህዝብ ባስቀመጠው ሰፊ የእፎይታ ጊዜ ውስጥ ሰላማዊ ትግላችንን አስመልክቶ ጥልቅ ፍተሻ እና ቀጣይ ጉዞን በሚመለከት ህዝብ አሳታፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የፍተሻው አበይት ውጤት የሚጠቁመው ያነሳናቸውን ሶስት ጥያቄዎች ለማስመለስ የአቅምም ሆነ የአካሄድ ጉድለት አለመኖሩን ነው፡፡ በተቃራኒው ያለማቋረጥ እየደረሱ ያሉት የመብት ጥሰቶች አንድ ህዝብ ሊያነሳቸው ከሚችላቸው የሰላማዊ ትግል አጀንዳዎች ትልቁን ለማንሳት የሚያስገድዱ ነበሩ፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ግን ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ብሶት መርሁን እንዳይስት አላደረገውምና ለጥያቄዎቹ አለመመለስ ጥያቄዎቹ የቀረቡበትን አግባብ እና የቀረቡለትን አካል መፈተሽ እንደሚያስፈልግ የጋራ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በነዚህ ህዝብ አሳታፊ ፍተሻዎች እና የቀጣይ ጉዞ የማስቀመጥ ስራ የትግል ጥያቄዎቻችን አንድ... ሁለት... ሶስት... እየተባሉ ተነቅሰው የሚወጡ፣ በጊዜ እና በቦታ የተገደቡ ውስን ነጥቦች አይደሉም፡፡ ይልቁንም አስፈላጊው ነገር የችግሮቻችንን ምንጭ ታሳቢ ያደረገና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚካሄድ ሁሉን አቀፍ ጉዞ መሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡

የሰላማዊ ትግላችንን ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መነሻ የሆነው እውነታ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ባለፉት ሁለት አመታት የከፈለው መስዋእትነትና ያዳበረውን አንድነት፣ ጥንካሬ፣ ትእግስትና ታዛዥነት በመጠቀም የበለጠ ተጠቃሚና ዘላቂ ወደ ሆነ ትግል ማሸጋገር መቻሉ ሲሆን በዝርዝር ድግሞ እንደሚከተለው ሊቀመጥ ይችላል፡-

•ሙስሊሙ ማህበረሰብ እየከፈለው ያለውን መስዋእትነት የበለጠ ውጤት-ተኮር ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ ስልቶችን በመንደፍ ሃይማኖታዊ መብታችንን ለማስከበር፣

•ህብረተሰቡ የታገለለት ዓላማ አካሄድ ሰላማዊ፣ ነገር ግን የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣

•እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት ሰፊና ዘርፈ-ብዙ ፍላጎቶችን ሊሸፍን በሚችል መልኩ እንዲሆን ለማመቻቸት፣

•ሁሉም የህብረተስብ ክፍል ትዕግስትና ጥንካሬ ተላብሶ እንደየዘርፉ የሚቻለውን እንዲያበረክት በር ለመክፈት፣

በእነዚህ መነሻዎች የሚቃኘውን የህዝበ ሙስሊሙን ቀጣይ ሰላማዊ ትግል አስመልክቶ ከፊታችን ባሉት ተከታታይ ሳምንታት ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና የህዝብን አመለካከት መልሶ ለህዝብ የማንፀባረቅ ሰፊ ስራ ይኖራል፡፡ በዚህ ስራ ላይ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ ትንተናዎችን በመስራት፣ ብዥታዎችን በማጥራት እና ለተግባራዊነታቸው በሙሉ አቅም በመስራት ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ እና የጀመርነውን ሰላማዊ ትግል ከጫፍ ለማድረስ የማይተካ ሚናውን እንደሚወጣ ይጠበቃል!

የትግል አቅጣጫ ማስገንዘቢያ መልእክቱን የድምጽ ትረካ ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡-
http://goo.gl/H2JjNn

ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!


No comments:

Post a Comment