Tuesday, April 29, 2014

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል መሪ የሆነው ''ድምፃችን ይሰማ'' የፌስቡክ ፔጅ

 ለአዲሱ የትግል ምዕራፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ ጀመረ!!!

''ድምፃችን ይሰማ'' አዲሱን የትግል ምዕራፍ አስመልክቶ ህዝበ ሙስሊሙ  የጋራ

 ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል::

መልዕክት ቁጥር 2 እነሆ! 

#EthioMuslimStruggle 
አዲሱን የትግል ምእራፍ አስመልክቶ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን የተላለፈ መልእክት - ቁጥር 2

የትግላችን ሂደት ለውጥ ግድ እንደሚል ማስረጃ ነው!
እሁድ ሚያዝያ 19/2006

ላለፉት ሁለት አመታት አንግበን የተነሳናቸው ሶስቱ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ደከመን ሰለቸን ሳንል በትዕግስት እየታገልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚሁ ያሳለፍናቸው የትግል አመታት ሂደታቸው ፍፁም ያማረ ቢሆንም ሶስቱን ጥያቄዎች ማስመለስን ገደብ አድርገን የተጓዝናቸው የትግል ጎዳናዎች ግን የምንፈልገው ቦታ ሊያደርሱን አልቻሉም፡፡ መንግስትም ጉዳዩን አጢኖ እልባት እንዲያገኝ ከመትጋት ይልቅ በአጉል ስም ማጥፋት ተጠምዶ ትግሉን በሀይል ለማስቆም እየባተለ ይገኛል፡፡ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሀይል እርምጃው ሳይገታው ‹‹ጥያቄዎቹ አለተመለሱም›› ሲል ትግሉን ቢቀጥልም የመንግስት አፀፋ ግን ለሞት እና ለጅምላ እስር ዳርጎታል፡፡ ቀን በቀን በተተካ ቁጥር የመንግስት እምቢተኝነትና የሚወሰደው እርምጃ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ትግሉ ከተጀመረበት ቅፅበት አንስቶ ባሳለፋቸው ሂደቶች የተከፈሉት ከፍተኛ መስዕዋትነቶች በርካታ የድል ፍሬዎችንም አስገኝተዋል፡፡

የትግላችን ሂደት በመስዋዕትነትና በድል ፍሬዎች መሀል እየፈሰሰ ይገኛል፡፡ እነዚህ መስዕዋትነቶችም ሆነ ፍሬዎች የትግሉን አቅጣጫ የማስመርም ሆነ የማስቀየር እምቅ ሀይል ተሸክመዋል፡፡ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉት የተጠኑ፣ አንዳንዴም የስማ በለው እርምጃዎች የጥንካሬን እንጂ የተስፋ መቁረጥን በር ሊከፍቱ አልቻሉም፡፡ የሀሰት ውንጀላው፣ ስም ማጥፋቱ፣ መስጂድ ነጠቃው፣ ጤናማ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎቹን ማፈኑ ፍርሀትን ሳይሆን ትግሉን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ቁጭትና ጥንካሬዎችን ፈጥሯል፡፡ ከጀመዓ፣ ከብሄር፣ ከአካባቢ፣ እንዲሁም ከኑሮ ደረጃ የልዩነት ማዕቀፎች በመውጣት ለትግሉ ጉዞ ምቹ ከባቢን የሚፈጥር አንድነት በዙሪያችን ተፈጥሯል፡፡

ያለፉት ሁለት አመታት የትግላችን ሂደት መገለጫ የሆኑት መስዕዋትነትና የድል ፍሬዎቹ ያዳበሩት አንድነት፣ ጥንካሬ፣ ቁርጠኝነት፣ ትዕግስተኝነት እና ታዛዥነትን በመጠቀም ሙስሊሙ ህብረተሰብ እየከፈለ ያለውን መስዕዋትነት የበለጠ ውጤት ተኮር ወደሆነና ዘላቂነት ወዳለው የትግል ምዕራፍ ማሸጋገር እና የአቅጣጫ ለውጥ ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

የአቅጣጫ ለውጡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በገዛ ሀገሩ መብት ጠያቂ ያደረጉትን እንቅፋቶችን ጥሶ በማለፍ በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገቶችና ለውጦች ላይ ንቁ ተሳትፊ እንዲሆን የአመለካከት ለውጥ በመፍጠር፣ የታገለለትን አላማ ሰላማዊ፣ ነገር ግን የተሟላ በማድረግ፣ እየተከፈለ ያለውን መስዕዋትነት ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶችን ሊሸፍን በሚችል መልኩ በማዋል፣ እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ትዕግስትና ጥንካሬ ተላብሶ እንደየዘርፉ የሚቻለውን እንዲያበረክት የሚያስችል በር የሚከፍት እንዲሆን የትግላችን ሂደት ያስገድዳል!

የትግል አቅጣጫ ማስገንዘቢያ መልእክቱን የድምጽ ትረካ ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡-
http://goo.gl/VZLYjv

ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment